"
THE FORMER ETHIOPIAN NAVY MEMORIAL WEBSITE
  • THE FORMER ETHIOPIAN NAVY WEBSITE
  • ገጽ2
  • ገጽ3
  • ገጽ4
  • ገጽ 5
  • ገጽ 6
  • ገፅ 7

ዜና እረፍት

27/2/2017

0 Comments

 
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሙዚቃ ክፍል የባስ ጊታር ተጫዋችና ድምጻዊ ባለሙያው ማስተር ቺፍ ቴዎድሮስ አበበ አረፉ።
ማስተር ቺፍ ቴዎድሮስ አበበ ( 1952 INTAKE) የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ካፈራቸው ምርጥ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችና በተለይም የኦሮምኛ ዘፈኖችን የሚጫወቱ መርከበኛ ነበሩ። በዘመነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በታላቋ ጦር መርከብ ኢትዮጵያ የረጅም ጉዞ ( CRUSING) ጉብኝት ለማድረግ ዓለምን ሲዞሩ የሃገራችንን ባሕል በውተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያስተዋውቁ የነበሩ የባሕር ኃይላችን ከነበሩት WORLD CLASS ሙዚቀኛ ነበሩ። ማስተር ቺፍ ቴዎድሮስ አበበ ባለትዳርና የልጆች አባት ነበሩ።
ለመላው ቤተሰብ ፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይል አባላት እግዚአብሔር አምላካችን መጽናናትን ይስጥልን
0 Comments

ክቡር ኮማንደር ታመነ ጃለታ ማን ነበሩ? ( Click here to comment)

15/8/2016

1 Comment

 
Picture
እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባል የነበረ መኮንንም ይሁን የበታች ሹም የኢትዮጵያ ባሕር ኃይላችንን ትዝታ በተመለከተ ሁሉም የራሱ PERCEPTION ይኖረዋልና በዚህ የባሕር ኃይላችን መታሰቢያ ዌብሳይት የሚሰማኝን ለሕዝብ በንባብና ከየአባሎቻችን ያገኘኋቸውን ፎቶግራፎች በመለጣጠፍ ለማሳየትና ለማስነበብ እየጣርኩ ነው። ክቡር ኮማንደር ታመነ ጃለታን በቅርብ ባላውቃቸውም በየጊዜው ወሳኝ ለሆኑ ከሌሎች የጦር ኃይሎች ማለትም ከምድር ጦርና ከአየር ኃይል ጋር በሕብረት ለሚደረግ ዘመቻዎች የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ እውቀታቸውን በሥራ እንዲያውሉ በጣም ከሚተማመኑባቸው ምርጥ መኮንኖች አንዱ ስለመሆናቸው በጦር መርከብ ላይ ነባር የሆነ ሠራዊት ሁሉ ያውቃቸዋል።
ኮማንደር ታመነ ጃለታ የተወለዱት በወለጋ ክፍለሃገር ሲሆን በኢትዮጵያ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ማገልገል የጀመሩት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1950ዎቹ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ነበር፡ በተዋጊ አይሮፕላን አብራሪነት በመኮንነት ተመርቀው ከ 1,000 ሰአት በላይ በረዋል። በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተሰናበቱ በኋላ እንደገና በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ በእጩ መኮንነት እንደ ኢትዮ አቆጣጠር በ1959 ዓም ለ 4 ዓመታት በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኮሌጅ በ NAVAL MARINE NAVIGATION EXCUTIVE OFFICER ሙያ ተምረው ከተመረቁ በኋላ ወያኔ መላውን የጦር ኃይል እስካፈረሰ ዘመን ድረስ ሃገራቸውን በቅንነት ፤ በጀግንነት፤ ያገለገሉ ምሁር ነበሩ።
ኮማንደር ታመነ ጃለታን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ልዩ የሆነ ከባሕር ወደ መሬት ለምድር ጦሩ የመድፍ ድብደባ እና ባሕር ወለድ ኮማንዶ ጦር የማውረድ ድጋፍ አስፈላጊና ወሳኝ ጥያቄ ከምድር ጦር ዘመቻ መምሪያ ከመጣ እቅድና ዘአመራሩ የሚሰጠው ለርሳቸው ሲሰጥ እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነበር።
-በአንድ ወቅት ያው እንደሚታወቀው የሻቢያ የኮማንዶ ጀልባአዛዥና ለወንብድና የሚያሰማራቸው ራሱ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ባልደረባ የነበረ ነውና፡ የተወሰኑ የሻቢያ ኮማንዶ ጀልባዎችን ምጽዋ ባሕር ኃይል መደብን እንዲደበድቡ እኩለ ሌሊት ላይ ይልካቸዋል። የሻቢያ ጀልባዎች ላይ የሚተክሏቸው የጦር መሳሪያዎች ባለ 14.5 ሚሊ ሜትር መትረየስና አሜሪካ ሥሪት Recoil የሌለው ( የማይራገጥ መድፍ) 106 ሚሊ ሜትር የቤኤም 21 ሮኬት መወንጨፊያውን ነጣጥለው ከ2 እስከ 3 ቧንቧ ( Barrel) አንድ ላይ በመግጠም በመኪና ባትሪ መወንጨፍ እንዲሁም በትከሻ የሚተኮስ ጸረ ታንክ ሮኬት ላውንቸር ብቻ ነው። እነዚህ የጦር መሣሪያዎች የጦር መርከብን የማስመጥ ኃይል የላቸውም። ምናልባት ተሳክቶላቸው የጦር መርከቡን ሞተር ክፍል ካልበሱ በስተቀር። ይህም ሆኖ ተሳክቶላቸው አያውቁም፡ በሬድዮ ፕሮፓጋንዳ ግን መላውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የጦር መርከበ እንዳሰመጡ ይለፈልፍልፉ እንደነበር አይረሳም።
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ሻቢያ የባሕር ወንበዴ ጀልባዎችን መሬት ጥግ ጥግ እየቀዘፉ እንዲጓዙና ምጽዋ ባሕር ኃይል መደብን እንዲያጠቁ ይልካቸውና በወቅቱ የሰሜን ባሕር ኃይል እዝ ዘመቻ መምሪያ መኮንኑ ኮማንደር ታመነ ጃለታ ነበሩና ከእኩለ ሌሊት በኋላ ኢላማቸው ምን እንደሆን የማያውቁት ወንበዴዎች ተኩስ ከፈቱብን፡ በወቅቱ እራሴ የነበርኩት ፈጣን አጥቂ ጦር መርከብ FMB-162 ላይ ነበርና በወቅቱ ለሠራዊቱ ከወታደራዊ መረጃ በደረሰው መረጃ መሠረት FIRST DEGREES OF REDINESS ተእዛዝ መሠረት ለማንኛውም በማለት የጦር መርከቧ መኝታዬ ላይ ጫማዬን በማውለቅ ብቻ ነበር ጋደም ያልኩትና ከእኩለ ሌሊት በኋላ ላይ ዘብ ላይ የነበረ ብሔራዊ ወታደር መኝታ ክፍሌ ውስጥ መጥቶ ስሜን በመደጋገም ፒኦ ፍሬሠናይ ፤ እየተተኮሰብን ነው በማለት ጮኸ ፡ ጊዜ ሳላባክን ጫማዬን አድርጌ ወደ ውጭ መሪ ክፍል ስወጣ የመርከቧን MAST ላይ አንድ ጥይት ጭሮ አለፈ። የጦር መርከባችን ማሪን ኢንጂነሮች ጁኒየር ሌፍትናንት ጋሻው አበራ ፤ ፒኦ አበራ ነገዎ፤ ፒኦ መዝገበ እምብዛና ፒኦ ቦጋለ በየነ ፍጥነታቸው ለጉድ ነበርና 3ቱንም የመርከቧን ሞተር እንዳስነሱ ቶኪቻው የጦር መርከባችን አዛዥ ሌፍትናንት ጨዋቃ ሚደቅሳ በፍጥነት ከነበርንበት FSS Jetty ለቀን ስንወጣ፤ ፒኦ ፍሬሠናይ LOAD BOTH GUNMOUNTS, COMMENCE FIRE WHEN YOU SEE THE TARGET አለኝ። ምክንያቱም ከወደብ የምንወጣበት ግራና ቀኝ መሬት ነው ፤ ምናልባትም ከፊታችን ጀልባዎቹ ሊኖሩ ይችላሉ በማለት ነበር። የኛ ጦር መርከብ ሬዳር የራሽያ ስለሆነ በጥራት ለማሳየት ጊዜ ስለሚወስድበት ኮማንደር ታመነ ጃለታ ባሕር ላይ በቅኝት ለነበረችው P-204 አዛዥ ለሌፍትናንት ስለአባት ( TIGER) ባሕር ላይ የሚታዩትን ኢላማዎች POSITION ንገረኝ ባሉት መሠረት የ P-204 አዛዥ በፍጥነት ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየሸሹ መሆናቸውን በሬድዮ ሲያስተላልፉ የኛ ጦር መርከብ ፍጥነት ስለነበራት በሬዳራችን ማየት እንደቻልን፡ ኮማንደር ታመነ ዓላማቸው ሁሉንም ወንበዴዎች በሕይወት ለመያዝ ነበርና ተከተሏቸው ብቻ ነበር እዝ የሚሰጡትና ለካስ ከኋላችን በፈጣን ጀልባዎች ማሪን ኮማንዶና ማሪን ዳይቨርስ ልከው ነበርና ወንበዴዎቹ ደግሞ የመረጡት ሽሽት ጀልባዎቹን መሬት አስነክተው ማምለጥ ነበርና እንደተገመተው ጀልባዎቹን AGROUND አድርገው ሲሰወሩ ለኛ ጦር መርከብ የመሳሪያችን ርቀት አካባቢውን መቆጣጠር ስለሚችል የ2 ኪሎ ሜትር ርቀት ኢላማ ስለተሰጠኝ ጥቂት ጥይት ለማሸበር ብቻ መሬቱ ላይ ተኮስኩ። ወዲያውኑ የኛ አንድ ጓድ ማሪን መሬቱ ላይ ወርደው አንዱ ብቻ እጅ አልሰጥም ብሎ ሲታኮስ ገድለው ሌሎቹን ማርከው እኛም 3 የሻቢያ ጀልባ ማርከን ጎትተን ምጽዋ  ወደብ ገባን። በወቅቱ አንድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል MI 24 ሄሊኮፕተር እግረኛ ወንበዴ ሊኖር ይችላል በማለት አካባቢውን ሲቃኝ ነበር፡፤
-- ሌላው ደግሞ ፡ ደቡብ የመን ከኢትዮጵያ ጋር የመረዳዳት የጦር ቃል ኪዳን ነበረንና በአንድ ወቅት በሶቪየት ራሽያኖች አቀነባባሪነት በመሪያቸው " በፕሬዚዳንት አሊ ናስር " ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎ የጦር ኃይሉ ለ 2 ተከፍሎ እርስ በርስ ሲታኮስ የየመን ባሕር ኃይል ጦር መርከቦች ጥቂቶቹ እኛው ጋር አሰብ መጡ። ፕሬዚዳንት አሊ ናስርም አምልጠው አዲስ አበባ ገብተው ነበርና ከሃገር መከላከያ ሚንስትር ዋናው ግዳጅ የተሰጠው ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ነበር። ለግዳጅ የተዘጋጁት ጦር መርከቦች 1ኛ FRIGATE- 1617, LCT 1037 ባሕር ወለድ ኮማንዶ ጦር የጫነች ምድረነክ ጦር መርከብ፤LCT -1036 ታንኮችና ምድ ጦር ሠራዊት የጫነች ፤ FMB-160 እራሴው በ CHIEF GUNNER የነበርኩባት ነበር፡ የአጠቃላይ እዝ የተሰጠው ለኮማንደር ታመነ ጃለታ ነበር ፡ ጉዞው ተጀመረ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ደቡብ የመን ላይ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገው በሶቪየት ሩሲያኖች መሆኑን አላወቀም፡፤ ጉዞ ጀምረን ሳለ ዘመቻው ስም ባይኖረውም መርከበኛው ወዲያውኑ ነው " ዘመቻ ናስር " ማለት የጀመረው። ባበኤል ማንዳብ ከመድረሳችን አስቀድሞ የነበረው ማዕበል ለጉድ ነበርና ታንክ የጫነችው ምድረነክ ጦር መርከብ 1036 ከፊት ያለው RAMP በማእበሉ ሃይል ተገንጥሎ ወደቀ ። ውሃ ወደ ጦር መርከቧ ቢገባም የፈረንሣይ ሥሪትና አሰራሯ ምቹ ስለነበር ብዙ እግረኛ ሠራዊት ብትጭንም ያለምንም ጉዳት ነበርችና በአጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግሥት በራሽያኖች አቀነባባሪነት መሆኑን ስለ መፈንቅለ መንግሥቱ ስለተረዳ ሁሉም የጦር መርከብ በአስቸኳይ ወደ አሰብ ወደብ ተመለሱ ተብሎ በሬድዮ መለእክት ተመለስን።
ኮማንደር ታመነ ጃለታ ምንጊዜም የማይረሱና ለወሳኝ የዘመቻ እቅዶች ቢጠሩም በተለያዩ የጦር መርከቦች ላይ በዋና አዛዥነት ሃገራቸውን ያገለገሉ ምርጥ መኮንን ነበሩ።  ፎቶግራፋቸውን ባለማግኘቴ በአጋጣሚ የስፖርት ቱታ ለብሰው ከጦር መርከብ አባሎች ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ ነው የለጠፍኩት።
ክቡር ኮማንደር ታመነ ጃለታ በአደረባቸው ሕመም ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1985 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል። እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን።

1 Comment

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ማሪን ኮማንዶ ( Click here to Comment)

21/5/2016

1 Comment

 
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ማሪን ኮማንዶ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1958 ዓም ተቋቋመ። የመጀመሪያዎቹ የማሪን ኮማንዶ አባላት በእሥራኤል ሃገር እና ከዚያም በብሪታኒያ ሮያል ማሪን ኮማንዶ አሠልጣኞች ሰልጥነው ከተመለሱ በኋላ የባሕር ኃይሉ የራሱን የማሪን ኮማንዶ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በኤርትራ እምባቲካላ በሚባለው ቦታ መሠረተ። ሥልጠናው ሲመሠረት ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የእሥራኤል ማሪን ኮማንዶ የግሪን ቤሬት ማሰልጠኛ ምሩቅ ስለነበሩ የማሪን ኮማንዶ አዛዥ ሆነው ተሾሙ።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ወደ እሥራኤል ሃገር ለማሪን ኮማንዶ ከመላካቸው በፊት በሓረር ጦር አካዳሚ በመጀመሪያ የ 4 ዓመት የአካዳሚክስና የወታደራዊ ሳይንስ ተምረው ፤ በአሜሪካን ሃገር በታወቀ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርትና እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማእረግ የተመረቁ ምሁር ናቸው።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ማሪን ኮማንዶ አባላት በወታደራዊ ግዳጅ ዘመቻ በቀይ ባሕር ደሴቶች ላይ በማድፈጥ በተለያዩ ጊዜያት ያለምንም ተኩስ በኮማንዶ ታክቲክ ብቻ ሻቢያ የጦር መሳሪያና ትጥቅ ለማመላለስ ወንበዴዎቹ ከየአረብ ሃገራት ሲመላለሱ የሚደበቁበት ደሴት ላይ በማድፈጥ ከነሕይወታቸው በመያዝ ተደጋጋሚ አኩሪ ገድል ፈጽመዋል።
የማሪን ኮማንዶ አባላት ግዳጃቸው በባሕር ወለድ LCM ( Landing Craft Marin) ጀልባዎች መሬት ላይ በመውረድ የሻቢያ ደፈጣ ተዋጊዎችን የሚማረከውን ማርከው ተኩስ የከፈተባቸውን ገድለውና፤ ተሰውተው ስለ ኢትዮጵያ ሃገራችን አንድነት በሚገባ ተዋድቀዋል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1969ዓም የሶማሊያ ግዙፍ ሠራዊት ሃገራችን ኢትዮጵያን በሓረርጌ እና በባሌ ክፍለሃገራት 750 ኪሎ ሜትር በወረራ በያዘብን ወቅት፡ የማሪን ኮማንዶ መኮንኖች የፓራ ኮማንዶና የሚሊሺያው ሠራዊትን በማዝመት ታላቅ ገድል የፈጸሙ ውድ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በምሥራቅ ጦር ግምባር ከዘመቱት ጥቂቶቹ ፦ ሌ/ኮማንደር መሰለ ደሥታ ፤ ሌ/ኮማንደር ተስፋዬ ውዴ፤ ሌ/ኮማንደር ፋንቱ፤ ሌፍትናንት መኩሪያ ዲዲማ፤ ሌ/ኮማንደር አለማየሁ ጆቴ እና ሌፍትናንት ዋቅጋሪ አሞሳ እንዲሁም ሌሎችም ስማቸውን የማላስታውሳቸው የባሕር ኃይል አባላት ናቸው።


የአየር ወለድ ክፍለጦር ከ1969 እስከ 1970ዓም ሲፈርስ የማሪን ኮማንዶ ክፍልም ፈርሶ እንደገና እነደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1973 ዓም አየርወለድ ሲመሠረት የማሪን ኮማንዶ ክፍልም ተቋቁሞ፡ በአየርወለድ የኮማንዶ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በሰሜን ኮሪያ የቴኳንዶ ወታደራዊ አሠልጣኞች ሠልጥነው፡ እንደቀድሞዎቹ ማሪኖች አዲሶቹም በተለያዩ የቀይ ባሕር ደሴቶች ላይ በማድፈጥ የሻቢያን ስንቅና ትጥቅ በመማረክና፡ የጦር መርከቦች የባህር ወንበዴዎችን አባረው ለመምታት ሲከታተሉ ጀልባቸውን ጥለው ወደ መሬት አስነክተው የፈረጠጡትን የሻቢያ ወንብዴዎችን በከባሕር ጠለቅ ኮማንዶ ጋር በመተባበር በ ZODIAC ጀልባ
መሬት ላይ ወርደው ከነሕይወታቸው ማርከዋል።
የማሪን ኮማንዶ አባላት በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ፡ ቀደም ብሎ በ SPECIAL FORCE ኮማንዶ የሰለጠኑት የማሪን ኮማንዶ አባላት ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም፡ በሚመሩት የአይሮፕላን ጠለፋ እንዳይደረግ በ ANTI HIJACKER የስውር ጥበቃ በማድረግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድም ጊዜ አይሮፕላኖቻችን እንዳይጠለፉ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።


ሳይጻፍ ቀረ የምትሉት ካለ የማሪን ኮማንዶ አባላት በ Facebook አካውንቴ በ Message በኩል ብትልኩልኝ EDIT በማድረግ አስተካከለዋለሁ


በግዳጅ ላይ ስለሃገራችን አንድነት የተሰዉትን አምላክ እግዚአብሔር ነፍስ ይማርልን፤ በሕይወት ያሉትንም እድሜ ይስጥልን
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!



1 Comment

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ባሕር ጠለቅ ኮማንዶ ( Click here to comment & Read comments)

6/12/2015

0 Comments

 
የባሕር ጠለቅ ኮማንዶ
ስለ ባሕር ጠለቅ ኮማንዶ የጦርነት ግዳጅ ሙያዬ ባይሆንም ከከፍተኛ የባሕር ኃይል መኮንን መምሕራኖቼ ከተረዳሁትና ራሴም ካየኋቸው፦
የባሕር ጠለቅ ኮማንዶ ስልጠና ዋናውን ወሳኝ የባሕርም ይሁን በባሕር ጠረፍ አካባቢ ወሳኝና በጥንቃቄ የተሰላ ግዳጅ ይወጡ ዘንድ ማንም ወታደር ተሰጥቶት የማያውቀውን ኃላፊነት ወስደው ለዋናው ተዋጊ፡ ለጦር መርከቦችም ይሁን ለባሕር ወለድ ጦር ማሪን ኮማንዶ የውጊያ አመቻች አብሪ እንደመሆናቸው መጠን በአእምሮ አስተሳሰብና በሰውነት ጠንካራ እንዲሆኑ ስልጠናው በጣም በጣም ከባድ ነው።
ከጣሊያንኛው ቃል Uomorana ከሚለውና በጠለቃ ወቅት ከሚለብሱት ልዩ ጠንካራ TIGHT ልብስና የቀዘፋው ጫማቸው የተነሳ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ FROGMEN ተብሏል።
በሲቪሉ የ DIVING CLUB ስፖርት ማሕበርም SCUBA DIVING ትእብሎም ይጠራሉ።
በአሜሪካን ባሕር ኃይልም NAVY SEALS በመባልም ይጠራሉ።
- የባሕር ጠለቅ ኮማንዶ ስልጠና በባሕር ውስጥ እጃቸው ላይ እንደ ሰአት ባሠሩት የማግኔቲክ ኮምፓስ የረጅም ርቀት የባሕር ውስጥ ለውስጥ ዋና በምጓዝ ጠላት ያጠመደውን የባሕር ውስጥ ፈንጂ ( MOORED MINE) ማምከን
- የጠላት የጦር መርከብ የሚመጣበትን አቅጣጫ ( COURSE) ተነግሯቸው የባሕር ውስጥ ፈንጂ የማጥመድ ግዳጅ ይወጣሉ።
- ልክ እንደ አየር ወለድ ከአይሮፕላን ዘለው ባሕር ውስጥ በመግባት የተሰጣቸውን ሚሽን ይወጣሉ።
- የባሕር ወለድ ማሪን ኮማንዶ ጦር በምድረነክ የጦር መርከብ ወደ መሬት ሠራዊት ለማውረድ ከመጠጋቱ አስቀድሞ በባሕር ውስጥ ለውስጥ ተጉዘው የባሕር ጥልቀቱን የሚለኩና በአካባቢው ስላለው የጥልቀት ውስጥ መረጃ ድንጋያማ፤አሸዋማ ወይም ቦታው አመቺ መሆኑንና አለመሆኑን መረጃ ይሰበስባሉ።
- የጠላት ሃገር ወደብ አካባቢ ከፈጣን ጀልባቸው ዘለው  ውስጥ ለውስጥ ተጉዘው በጠላት የጦር መርከብም ይሁን በወደብ አካባቢ ባለው ወታደራዊ ዒላማ ላይ ፈንጂ በማጥመድ ጥቃት ያደርጋሉ።

ስለጠናው በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የደቡብ የመን ባሕር ኃይል የላካቸው 20 የሚሆኑ ሰልጣኞች ውስጥ ስልጠናውን ያጠናቀቁት 2 አባሎች ብቻ እንደነበሩ አይረሳኝም።
- ሌላው የደቡብ ሱዳን ነሳ አውጪ ጦር ከሰሚን ሱዳን ጋር በውጊያ ሳሉ ከታጋዮቹ መሃል ተመርጠው ምጽዋ ባሕር መደብ በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ባሕር ጠለቅ ኮማንዶ ሰልጥነው ኮርሱን ጨርሰው ወደ ሃገራቸው በተመለሱ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ሱዳን ወደብ ላይ በባህር ውስጥ ተጉዘው 2 የሱዳን ባሕር ኃይል የጦር መርከብ ማፈንዳታቸውን በጀርመን ሬድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ማዳመጣችንን አይረሳኝም።
ውድ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የባሕር ጠለቅ ኮማንዶ አባላት፡ ስለ ሃገራችን ኢትዮጵያ ላደረጋችሁት ውለታ የኢትዮጵያ አምላክ እድሜና ጤና ይስጣጭሁ። በግዳጅ ላይ ለተሰዉት መላው የኢትዮጵያ ወታደሮች ሁሉ፡ አምላክ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን።



0 Comments

 ክቡር ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ ማናቸው? እያንዱን ፎቶግራፍ ለማየት ፎቶውን  ይጫኑ ( Click here to comment & read comments)

28/11/2015

1 Comment

 

Picture
ክቡር ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ በኢትዮጵያ ሃገራችን ስማቸው በታላቅ ትሩፋት ከሚነሱ የኢትዮጵትያ ባሕር ኃይል ካፈራቸው የሃገራችን ባለውለታዎች አንዱ ታላቅ ክቡር ሰው ነበሩ። በውትድርናውም ሆነ በሲቪሉ ዓለም ሕይወታቸውን በሙሉ ከራሳቸው ይልቅ ለእናት ዓለም ኢትዮጵያ የተግባር ባለውለታ ክቡር ከፍተኛ መኮንን ነበሩ።
ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ መስከረም 22 ቀን 1934 ዓም በሓረር ከተማ ተወለዱ። አባታቸው አቶ ቦጋለ ጃቶ ነጋዴና እንዲሁም ኢትዮጵያ ሃገራችን በፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች ስትወረር በአርበኝነት ስለሃገራቸው እናት ኢትዮጵያ ፍቅር ዘምተዋል።
አባታቸው አቶ ቦጋለ ጃቶ ልጆቻቸውን በኢትዮጵያዊነት ሥነምግባር ማሳደጋቸውና ክቡር ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለም 5ኛና የመጨረሻ ልጃቸው እንደሆኑ በውጭ ሃገር ያሉ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አብራርተው እንደነበር አይዘነጋም።
ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ የከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ሓረር ከተማ ባለው፡ ራስ መኮንን ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሲመሠረት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1948 ዓም የመጀመሪያው እጩ መኮንኖች ከነበሩት አንዱ ነበሩ።
በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኮሌጅ አካዳሚ በነበሩ ወቅት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተለያዩ ሽልማቶችን ተቀብለዋል።
ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ታሪክ የመጀመሪያው የጦር መርከብ ካፒቴን ( THE FIRST ETHIOPIAN NAVAL OFFICER TO COMMAND THE FLAG SHIP OF THE NAVY) ሲሆኑ የጦር መርከቧም HMS ( ታላቋ ጦር መርከብ ኢትዮጵያ ) ነበረች።
ከዚያም በኋላም የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።
በዘመነ የደርግ ኢትዮጵያ መንግሥት ኮማንደር ዘለቀ " አጠቃላይ የባሕር ትርናስፖርት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለ 17 ዓመታት አገልግለዋል።" የሁለቱም የምጽዋና አሰብ ወደብና እንዲሁም በሃገር ውስጥ ያሉትን የጣና ጎርጎራ፤ ሻላ ፤ አቢያታና አርባ ምንጭ ያሉትን ሁሉ ዘመናዊ እንዲሆኑ ደከመኝ ሰለቸኝ፡ሳይሉ የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑና በተለይም የአሰብ ወደብ በዓለም አቀፍ እኩሌታ አገልግሎት እንዲኖረው ግዙፍ ክሬኖችና ለሠራተኞችም የመኖሪያ ቤቶችንና ልዩ የሆነ ክበብ በማሰራት የወደብ አገልግሎቱን ፈጣን ይዘት እንዲኖረው በሚያስደንቅ ሁኔታ ለውጠው እንደነበር አይዘነጋም።
እያንዳንዱ ሠራተኛ ኃላፊነቱን በተግባር ይወጣ ዘንድ የቅርብ ክትትል በማድረግ ይሰነፈውን በመገሰጽ፤ ጎበዙን በማበረታታት ሃገራችን ኢትዮጵያን ታላቅ ደረጃ አድርሰዋት ነበር።
ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ ከኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኮሌጅ አካዳሚ ተመርቀው ከወጡ በኋላ የተማሩት፦ በ USA አሜሪካን ሃገር SAN DIEGO NAVAL ACADEMY እና በእንግሊዝ ሃገር BRITISH NAVAL ACADEMY IN DARTMOUTH የተማሩትም ሙያ NAVAL WARFARE AND EXCUTIVE / LEADERSHIP , ከዚያም  በ BIRMINGHAM UNIVERSITY POST GRADUATE በ DIPLOMA IN THE SOCIAL SCIENCE AND ARTS.ነው።
ክቡር ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ ስለሃገራቸውና ወገናቸው ውለታና የማያሰልስ የአስተዳደራዊ ብቃታቸውና ጥረታቸው ፤ ስለወደቦቹ ዘመናዊነት ፍጥነት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በአንድ ወቅት ሲናገሩ "" ኢትዮጵያ የኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ ተመሳሳይ የተግባር ሥራ አስኪያጅ ቢኖራት የተ በደረሰች ነበር "" በማለት አድናቆታቸውንና ምሥጋናቸውን ተናግረው እንደነበር በቅርብ የሰሙ ምክትሎቻቸው ሲናገሩም ሰምተናል።

ክቡር ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ እንደ አውሮፓ አቆጣተር JUNE 8 2009 እኩለ ቀን ላይ አርፈዋል።
ክቡር ኮማንደር ዘለቀ የ 2 ልጆች አባት ማለትም አሁን የአርበኞች ግንቦት 7 የውጭ፡ጉዳይ ኃላፊው የክቡር አቶ ነዓምን ዘለቀ እና የአቶ አድነው ዘለቀ እንዲሁም የልጅ ልጆቻቸው እምአእላፍ ነአምን እና ኢዮር ነዓምን አባት ነበሩ።
የኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማርልን።
አሜን።
1 Comment

    RSS Feed

Picture
Picture
  •  ክቡር ካፒቴን መርሻ ግርማ ፡ ከባሕር ኃይላችን ሲንየር የባሕር ኃይል መኮንኖች አንዱ ሲሆኑ፡ እውቀታቸውን ከድፍረታቸው ጋር በራስ የመተማመን ባሕርያቸው ጋር ከምክትል የጦር መርከብ አዛዥነት እሰከዋና አዛዥነት ሃገራቸው ኢትዮጵያን በጀግንነት አገልግለዋል። በባሕር ኃይል አባልነት ከተቀጠርን ጊዜያት አንስቶ በ1970 ዓም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የነበሩት አለቆቻችን ሲናገሩ፡ ጠላት የሻቢያ ጦር መላውን ኤርትራ ከአሥመራና ከምጽዋ በስተቀር በተቆጣጠረበት ወቅት፡ በምጽዋ አካባቢ የነበረው ጦር አፈግፍጎ በኢትዮጵያ የባሕር ኃይል መደብ በተጠጋበት ወቅት የባሕር ኃይላችንን የእግረኛ ጦር በማስተባበር መደቡ እንዳይያዝ የጦር መርከቦች የመድፍ ድጋፍ እየሰጡ እንዲዋጉ ሌትና ቀን በጀግንነት የመሩ እነደነበሩ በወቅቱ የነበሩት ይመሠክራሉ።

  • ከሃገር መከላከያና ከዋና የልዩ ልዩ ክፍል አዛዦች በአመራራቸው ላይ ተጽእኖ ሊያደርጉባቸው ሲሞካክሩ፡ ለማይመለከታቸው ነገር ሁሉ ተገቢ መልስ በመስጠት አመራራቸውን በተግባር ያሳዩ ውድ የኢትዮጵያ ሃገራችን ጀግና መኮንን ናቸው። በነበረው ስርአት ደስተኛ ባለመሆናቸውና ያልመሰላቸውን ነገር በድፍረት  ያለመቀበላቸው፡ ወደሚቀጥለው ማእርግ እንዲተላለፉ ያለመደረጉ፡ በተለይም የ1970 ው የአመራር ገድል የርሳቸው አመራር ሆኖ ሳለ፡ ሌሎች በሹመት ላይ ሹመት ሲደራረብላቸው የርሳቸውን ገድል ያዩ ሁሉ አለቆቻችን የሁልጊዜ ርእሰ ጉዳይ እንደነበር አይረሳኝም። ለወታደራዊ ከፍተኛ መኮንነታቸው ለተሰጣቸው ከባድ ኃላፊነት ከፍተኛ ጥንቃቄና በራሳቸው የሚተማመኑ ከመሆናቸው የተነሳ፡ ከምጽዋ ባሕር ኃይል መደብ ለሥራ ጉዳይ ወጥተው ሲመለሱ፡ በዋናው በር ላይ ያሉትን ዘቦች፡ እኔ እየነዳሁ ያለሁት መኪና መፈተሽ አለበት፤ ምናልባትም በጠላት ታፍኜ የባሕር ኃይሉ ግቢና በአካባቢው ያሉ የቆሙ ጦር መርከቦች ላይ ጠላት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በማለት ይናገራሉ፤ የጥቂት ስህተት ነገር፡ በጠላት መጠቃት እንደሚያመጣ ይናገሩና የሚያሳስቡና ባለግርማ ሞገስ ከፍተኛ መኮንን ናቸው።  ረጅም እድሜና ጤንነት እመኝሎታለሁ፡ ውድ ካፒቴን መርሻ ግርማ።

Picture
ክቡር ኮማንደር ማቴዎስ መኮንን ከባሕር ኃይላችን የማሪን ኢንጂነሪንግ ሲንየር መኮንኖች አንዱ ናቸው። ለሰባት አመታት ተኩል ባገለገልኩበት የ8ቱም ፈጣን አጥቂ ጦር መርከብ 111ኛ ስኳድሮን የማሪን ኢንጂነሪንግ ኮማንደር ሲሆኑ፡ የጦር መርከቦቹ ምንጊዜም ለግዳጅ ብቁ እንዲሆኑ፡ ከየጦር መርከቦቹ አባሎችን መርጠውና ሞባይል ቲም በማቋቋም የሶቪየት ሥሪት የሆኑትን የጦር መርከቦች ጥገና ሲያደርጉ ዕውቀታቸውን ሳይሸሽጉ በቲዎሪም ይሁን በተግባር ክልብ በሆነ ጥረት የሚያደርጉትን ሁሉ አብረዋቸው የሚሠሩት የማእርግ ጓደኞቼ ሁሉ በየዕለቱ ሲናገሩ የምንሰማው ሃቅ ነበር።


በተለይም የሶቪየት ጦር መርከቦች ኢንጂን EXPIRED DATE የተመደበለትና በአጋጣሚ ብልሽት ቢያጋጥመው እንኳን፡ እንደ ምራባውያኑ መለዋወጫ ተገጥሞለት እንደገና በሥራ ላይ እንዳይውል የተደረገ ስለነበር፡ ሁኔታው ከሚያሳስባቸው ቀዳሚ መኮንኖች አንዱ ስለነበሩ፡ አስታውሳለሁ በጦር መርከብ 162 ላይ GEAR BOX ላይ ችግር አለ በማለት SEALED ሆኖ የተገጠመውን ኢንጂን ከሌሎች የጦር መርከቦች ተፈታቶ ሜዳ ላይ ተቀምጦ ከነበሩት አስቸጋሪ የነበረው ውስብስብ በመፈታታት ለመርከባችን ጥገና አድርገው በብዙ ሚሊዮን ዶላር ሊያስወጣ የነበረውን ዋጋ ከአስተባበሩት የጥገና ቡድን ጋር ዓላማቸውን አሳክተዋል። ቀደም ብሎ ሁሉም የሶቪየት ጦር መርከቦች ነዳጃቸው በውድ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ስለነበር የሚገዛው፡ እንደሌሎቹ ከመራባውያን የተገዙት የጦር መርከቦች አሰብ ከሚገኘው የነዳጅ ማጣሪያ ነዳጃቸውን እንዲጠቀሙ፡ ከሌሎች መኮንኖች ጋር በመሆን ሁኔታውን አጥንተው ሃገራችንን ከኪሳራ ያዳኑና የሙያ አጋሮቻቸውና የማዕርግ ጓደኞቻችን፡ እውቀታቸውን በማካፈልም ሆነ ጉልበታቸውን ጭምር አብረው በመሥራት በተግባር  ሁልጊዜ በሚያደርጓቸው ከልብ የሆነ ትጋት፡ በማድነቅና በማክበር የሚያመሰግኗቸው ውድ የባሕር ኃይላችን ከፍተኛ መኮንን ናቸው።

 ---"""   ሌላው የእርሳቸው ትሩፋት፡ የባሕር ኃይላችን ጦር መርከቦች መደብ ወደ ዳሕላክ፤ ናኩራ ከተዛወረ በኋላ፡ በደሴቲቱ ላይ የውሃ ግድብ ባለመኖሩና በአካባቢው ያለው የባሕር ኃይልና የምድር ጦር ሠራዊት የውኃ ችግር በጣም የበረታበት ቦታ ስለሆነ፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእስራኤል ሃገር የቀይ ባሕርን የጨው ውኃ ወደ ንጹሕ ውኃ የሚለውጥ ( DISTLLING PLANT) ታላቅ ፕሮጀክት እቅድን በተመለከተ፡ ለቀናት ብቻ እዚያው እስራኤል ሃገር ከውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ቴክኒሺያኖች ጋር ሄደው በእስራኤሎች በተደረገላቸው የጥቂት ቀናት ማብራሪያ ብቻ፡ ወደ ውድ ሃገራቸው እንደተመለሱ የ DISTLLING PLANT ቀደም ብሎ በሃገራችን ያልነበረ ቢሆንም፡ አብረዋቸው ለማብራሪያው እስራኤል ሃገር የነበሩት፡ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሠራተኞች ግዙፉ ፕሮጀክት ግራ አጋብቷቸው፡ ኮማንደር ማቴዎስን የሚሳካ ይመስለዎታልን ጥያቄ ሲአያስከትሉ፡ በአጋጣሚ የመጣው መሣሪያ ሁለት ቢሆንም፡ አንደኛው በንግድ መርከብ ጭነት ሲመጣ በማዕበል የተጎሻሸመና የተጎዳ ቢሆንም፡ ኮማንደሩ ባላቸው የዕውቀትም ይሁን የራስ ተነሳሽነት ፅናት ተደማምሮ መሣሪያው እንዲሠራና  ሁሉም ነገር ተሳክቶ የሠራዊቱንም ይሁን የአካባቢውን ሕዝብ የውኃ ፍላጎት አሳክተዋል። ኮማንደሬ ረጅም  ዕድሜና ጤንነት እመኝሎታለሁ """"
።